ኢትዮጵያ ነገ ዜና|| የእንቦጭ አረምን ሙሉ በሙሉ በአንድ ወር ውስጥ ማጥፋት የሚያስችል መድኃኒት ተገኘ።
በፍጥነት በተለያዮ የሃገሪቱ ክፍሎች የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም በአንድ ወር ውስጥ ማጥፋት የሚያስችል እና በፈሳሽ መልክ የተሠራ መድኃኒት መሥራታቸውን የገለጹት የባህል ተመራማሪ መሪጌታ በላይነህ አዳሙ ናቸው።
ባህላዊ ሕክምና ሕመምን ከመፈወስ በተጨማሪ ማኅበራዊ ችግርን ለመቅረፍም ያገለግላል የሚሉት መሪጌታ በላይነህ፤ እርሳቸው የቀመሙት የእንቦጭ ማጥፊያ አሁን እየተተገበሩት ካሉት የተሻለ መፍትኄ የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል።
ለባህላዊ መድኃኒታቸው ከአዕምሯዊ ንብረት ፈቃድ ማግኘታቸውን የተናገሩት የባህል መድኃኒት ተመራማሪው በዋጋ ደረጃ አንድ ስኩዌር ሜትር ለመርጨት ከ30 እስከ 50 ብር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ምርምሩ ሠባት አመታትን መውሰዱንና ሌላው ዓለም ከባህላዊ ሕክምና በመነሳት ዘመናዊ ሕክምናን ማሳደጉን የገለጹት መሪጌታ፤ ኢትዮጵያ የቆየ ሥልጣኔና ብዝኃ ሕይወት ባለቤት እንደመሆኗ፣ ይህንን ትምህርትና ስልጠና ተጠቅሞ አዘምኖ እንደመጠቀም የባህላዊ መድኃኒት አዋቂን ማግለል ሁኔታ ይታያል፤ ይህ ደግሞ መፍትኄ ለማምጣት በጋራ እንዳንሠራ ያደርገናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ቻይናን መሰል ሃገራት የባህል መድኃኒቶች ብቻ የሚበቅልባቸው የእርሻ ቦታዎች መኖራቸውን ያመላከቱት የባህል መድኃኒት ተመራማሪው፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ይህ አሠራር ብዙም ትኩረት የማይሰጠው በመሆኑ በጉዳዮ ላይ ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ለሃገር በቀል እውቀትና መፍትኄ ቅድሚያ በመስጠትና ችግሮችንም ቅድሚያ ሰጥቶ ለመፍታት አገር በቀል እውቀቶችን መጠቀም እንደሚስፈልጋቸውም ገልፀዋል፡፡