ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተፈቀደላቸው በሙሉ፤ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድም ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።
ኢሰመኮ አቶ ልደቱን በመሚመለከት ባወጣው መግለጫ አላስፈላጊ እስር ማስቀረትና የዋስትና መብት ማከብር ያስፈልጋል ሲል ለሕግ አስፈጻሚዎች መልእክት አስተላልፏል።
ልደቱ አያሌው በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ መስከረም 12/2013 ዓ.ም ትዕዛዝ ቢሰጥም እስካሁን አለመፈታታቸውን ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ዋና ዋስትናው የፍርድ ቤት ውሳኔ መከበር መሆኑን በመግለጫው ላይ አስቀምጠዋል።
ልደቱ አያሌውን ጨምሮ በፍርድ ቤት ዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ታሳሪዎች በሙሉ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ሊፈቱ ይገባል ሲልም በእርሳቸው የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ያለውን አቋም ይፋ አድርገዋል።
በአንድ መቶ ሺኅ ብር ዋስ እንዲፈቱና ጉዳያቸውን ከውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት የተፈቀዳለቸው አቶ ልደቱ አያሌውን ፖሊስ አልፈታም በማለቱ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ማስገባታቸውን የተናገሩት ጠበቃቸው አቶ አብዱልጀባር ሁሴን ፤ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት መስከረም 12/2013 ዓ.ም አቶ ልደቱ በዋስ እንዲፈቱ ቢወስንም ፖሊስ “በአደራ ነው እዚህ የተቀመጡት” የሚል ምላሽ ሰጥቶ ሊፈታቸው ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
አቶ አብዱል ጀባር በትናንትናው ዕለት፣ መስከረም 14/ 2013 ዓ.ም የፍርድ ቤት ትዕዛዙን ይዘው ወደ ቢሾፍቱ ፓሊስ ጣቢያ ቢያመሩም ፖሊስ ሊለቃቸው ፈቃደኛ እንዳልሆነ አስረድተዋል።