ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የደመራ በዓል የማክበሪያ ስፍራ በአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስተባባሪነት ዛሬ መፀዳቱ ተነግሯል።
የከተማ አስተዳደሩ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለደመራ በዓል ማክበሪያ ዝግጁ እንዲሆን ለማድረግ ቃል በገባው መሠረት በተባለው ጊዜ ዝግጁ ሆኖ መቅረቡ ቢገለጽም፤ አሁንም በስፍራው ላይ ከፍተኛ የሆነ የቁሳቁስ እና የግንባታ ማሽኖች ክምችት መኖሩን ኢትዮጵያ ነገ መታዘብ ችሏል።
የደመራ ክብረ በዓል የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በውስን የእምነቱ ተከታዮች ተሳታፊነት እንደሚከበር እየተነገረ ቢሆንም፤ በመስቀል አደባባይ ላይ እነዚህ ውስን የተባሉ ሰዎችንም ርቀት በጠበቀ መልኩ በዓሉን የሚያስችል ቦታ እንዲለቀቅ ተደርጓል ወይ? የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ነጥብ ሆኗል።
ከፖለቲካ ትርፍ ጋር በተያያዘ ለወትሮው በመዲናዋ ወጣቶችና የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ይከናወን የነበረው የፅዳት ፕሮግራም በተመረጡ አደረጃጀቶች እንዲከናወን ከተደረገ በኋላ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በፅዳት ሥራው የተሳተፉትን እናመሰግናለን ሲሉ ተደምጠዋል።
የደመራ ክብረ በዓል የማክበሪያ ቦታውን የጸረ-ተህዋስ ኬሚካል ርጭት በማድረግ የማጽዳት መርሃ ግብርም የተከናወነለት ቢሆንም፤ በዓሉ ከሁለት ቀን በኋላ የሚከናወን እንደመሆኑ እስከዛ ድረስ ቦታው ተከልሎ ከእንቅስቃሴ ነፃ ሆኖ እንዲቀመጥ ከማድረግ ባሻገር፤ ተደጋጋሚ ርጭቶችም መከናወን አለባቸው እየተባለ ነው።
የደመራ ክብረ በዓል የማክበሪያ ስፍራ የጽዳት ዘመቻ ላይ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ከሁሉም ሃይማኖቶች የተውጣጡ ወጣቶች ፣ የፅዳት ሠራተኞች ፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።