ለደመራ መስቀል አደባባይ የሚወጣ ምዕመን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ተባለ

ለደመራ መስቀል አደባባይ የሚወጣ ምዕመን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር ወደ መሰቀል አደባባይ የሚመጣው ምዕመን አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጎ በክብረ በዓሉ ቦታ እንዲገኝ መልዕክት ተላለፈ።

ምዕመኑ ከሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርግና የበዓሉ ድምቀትም እንዳይጓደል በቤተክርስቲያኗ በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገለጸች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ሓላፊ፣ እንዲሁም የድሬዳዋና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የበዓሉ ተሳታፊዎች ቁጥር እንዲገደብ የተደረገው በኮቪድ-19 ወረርሽኝና  የመስቀል አደባባይ ወቅታዊ የማስተናገድ አቅም ምክንያት እንደሆነም አስረድተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲያግዝ የምዕመኑ ቁጥር እንዲወሰን የተደረገ ከመሆኑም ባሻገር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ ቤተከርስቲያኗ የተዘጋጀች ሲሆን፣ ምዕመኑም ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር መተግብር እንደሚገባ ተገልጿል።
በዓሉ ከመስቀል አደባባይ በተጨማሪ በየአብያተ ቤተክርስቲያኑ የሚከበር በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይህንንም ከግንዛቤ በማስገባት እራሱን መጠበቅ እንዳለበት የተናገሩት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፤ የመስቀል ደመራ በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ በመሆኑ በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱና ሥርዓቱ ሳይጓደል በደመቀ ሁኔታ መከበር እንዲችል አሰፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
የ2013 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን አሰመልክቶ ቤተክርስቲያኗ የወሰደችው እርምጃ የሚበረታታ ቢሆንም፤ በበዓሉ ላይ የሚገኙ ምዕመናን ሓላፊነት ግን ትልቁን ድርሻ የሚይዝ እንደመሆኑ ወረርሽኙን ለመከላከል የጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል የሚል መልእክት ተላልፏል።

LEAVE A REPLY