ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ደንበኞቹ በተለያዩ አጋጣሚ የሞባይል ስልካቸው በሚጠፋበት ጊዜ ስልክ ቁጥራቸውን ወዲያውኑ ባለማዘጋታቸው በሶስተኛ ወገን የቴሌኮም ማጭበርበር እየተከናወነ ነው ተባለ።
ተቋሙ እንደገለጸው ከሆነ ይህ ችግር ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ ይገኛል።
ከላይ ከተገለጸው ባሻገር ደንበኞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የስልክ መስመራቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸው የተነሳ ወንጀለኞች የስልክ መስመሩን ለተለያዩ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀሎች እየተጠቀሙበት ነው ሲልም የችግሩን አሳሳቢነት ገልጿል።
የሞባይል ተጠቃሚዎች ስልካቸው ሲሰረቅ ወደ ተቋሙ በመደወል በፍጥነት ማዘጋት አለባቸው ያለው ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዮ ዘመናዊ አማራጮች በሥራ ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል።