ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ እየተካሄደበት በሚገኘው ሀሙስ ዕለት ሌሊትም ተመሳሳይ እርምጃ በአማሮች ላይ መፈጸሙ ተነገረ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ በንገዝ በተባለ ቀበሌ ውስጥ መስከረም 14/2013 ዓ.ም ሌሊት ላይ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውም ታውቋል።
ታጣቂዎቹ ጥቃቴ የተፈጸመበት የበንገዝ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምለው፤ ቢያንስ 14 ሰዎች በጥይት መገደላቸውንና ከሰለባዎቹ መካከልም የአርሳቸው ወንድምም እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ ፤ በድጋሚ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ከማረጋገጡ ባሻገር፣ በስፍራው ያለው የፀጥታ ጉዳይ አሳሳቢ ነው ብሏል።
“ጥቃቱ የተፈጸመው ሌሊት 10 ሰዐት ነው፤ ምን እንደተፈጠረ ማወቅ አልቻልንም። የጥይት ተኩስ ብቻ ነበር በአካባቢው የሚሰማው፤ ብዙ ሰው ነው ያለቀው። የእኔ ወንድምም በጥቃቱ ተገድሏል” ያሉት ሓላፊው፤ እስካሁን በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ይህንን ጥቃት ማን እንደሚፈጽመው አልታወቀም ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሓላፊ የሆኑት አቶ መለሰ በየነ ሐሙስ ሌሊት የተፈጸመውን ጥቃትና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የተጠናቀረ መረጃ እንደሌላቸው ቢናገሩም፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ግን አርብ እስከ ቀኑ 8 ሰዓት ድረስ ባሰባሰበው መረጃ መሠረት15 ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን፣ ከእነርሱ ውስጥም 11ዱ ወንዶች 4ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ከአካባቢው የመንግሥት ምንጮች አረጋግጫለሁ ብሏል።