ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለአረጋውያን የነፃ ህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት አድርጊያለሁ አለ።
አረጋውያን የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የዕርቅ፣ የመቻቻል፣ የፅናትና የታማኝነት አርአያ እንደሆኑ የተናገሩት የሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ የዘንድሮ ዓለም ዐቀፍ የአረጋውያን ቀን ለአረጋውያን ክብር በመስጠት መስከረም 21 እንደሚከበር ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ በአረጋዊያን ላይ የፈጠረው በኢኮኖሚ የመገለል ስሜት ለከፍተኛ ችግር እንደዳረጋቸው የጠቆሙት ሚኒስትሯ ፤ ይህን ለማስቀረት ኅብረተሰቡ የቀደመውን የመረዳዳት እሴቱን አረጋውያንን በመደገፍ ወገንተኝነቱን እንዲያሳይም መልእክት አስተላልፈዋል።
የአረጋዊያንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የ10 ዓመት እቅድ በማዘጋጀት ለሚኒስትሮች ም/ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ አረጋዊያን ለሀገር የነበራቸውን በጎ አሻራ ለመዘከርም በዓሉ የፊታችን ሀሙስ መስከረም 21 ለ29ኛ ጊዜ እንደሚከበር ከወዲሁ ተነግሯል።