አፍሪካ እየተራባ ከሚሔደው የኮሮና ቫይረስ የሥርጭት ጠባይ አምልጣለች ተባለ

አፍሪካ እየተራባ ከሚሔደው የኮሮና ቫይረስ የሥርጭት ጠባይ አምልጣለች ተባለ

 ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አፍሪካ በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደታየው እየተራባ ከሚሔደው የኮሮና ቫይረስ የሥርጭት ጠባይ ማምለጧን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።
በአንድ ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ የአኅጉሪቱ ሞቃታማ እና ርጥብ የአየር ጠባይ ለዚህ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ የተገመተ ሲሆን፣ እስከ ትናንት ወዲያ አርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በአፍሪካ 34 ሺኅ 706 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
 በተሰበሰበው መረጃ መሠረት 1 ሚሊዮን 439 ሺኅ 657 ሰዎች እስከ አርብ ድረስ በአፍሪካ በኮሮና ተይዘዋል።
ይሄ አኃዝ ከሌሎች አኅጉሮች አኳያ አነስተኛ ነው ተብሏል። በልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ብቻ 203 ሺኅ 789 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና ከሠባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና መያዛቸውን የጆን ሖፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ቋት አረጋግጧል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ከኮንጎ ብራዛቪል ባወጣው መግለጫ “በአፍሪካ የኮቪድ-19 ስርጭት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ባለፉት ሁለት ወራት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነበር፤ ባለፉት አራት ሳምንታት 77 ሺኅ 47 ሰዎች በኮሮና መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን በቀደሙት አራት ሳምንታት 131 ሺኅ 647 ነበር” ሲል ገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ሓላፊ ማትሺዲሶ ሞቲ ወረርሽኙ በበረታባቸው አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት፣ ኬንያ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካ ባለፉት ሁለት ወራት በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም መቀነሱን ጠቁሟል።
ሮይተርስ ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ በከፍተኛ ብዛት ከተስፋፋባቸው 50 አገራት አንዷ ስትሆን፣በኢትዮጵያ እስከ አርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በአጠቃላይ 72 ሺኅ 173 ሰዎች በወረርሽኙ ሲያዙ 1 ሺኅ 155 ሰዎች ኮሮና ባስከተለው ሕመም ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ደቡብ አፍሪካ በኮሮና ክፉኛ የተጎዳች የአፍሪካ አገር ሆናለች። እስከ አርብ ድረስ በደቡብ አፍሪካ 667 ሺኅ 049 ሰዎች በኮሮና ሲያዙ 16 ሺኅ 283 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በአንድ ቦታ ተፋፍገው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ ሞቃታማው እና ርጥብ የአየር ጠባይ እንዲሁም ከአኅጉሪቱ የሕዝብ ቁጥር አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸው በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለመቀነሱ አስተዋጽዖ ሊኖራቸው እንደሚችልም ግምቱን አስቀምጧል።

LEAVE A REPLY