ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ቲክቶክ ከትናንት ምሽት ጀምሮ በአሜሪካ ሰዎች አውርደው እንይጠቀሙበት ገደብ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፤ የዋሽንግትን ዲሲ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ዳኛ ካርል ኒኮላስ እግዱን መሻራቸው ተሰማ።
ዳኛው ይህን ውሳኔ ባያስተላልፉ ኖሮ በአሜሪካ የሚገኙ አዲስ ተጠቃሚዎች ቲክቶክን ከአፕል እና ጎግል ፕሌይ ስቶር ላይ አውርደው መጠቀም አይችሉም ነበር ተብሏል።
በተጨማሪም መተግበሪያውን በስልኮቻቸው ላይ ጭነው የሚገኙ ተጠቃሚዎችም መተግበሪያውን ማሻሻል አይችሉም መባሉ ተሰምቷል።
ዳኛ ካርል ኒኮላስ ትናንት ምሽት የአሜሪካ መንግሥት ያስተላለፈውን ውሳኔ የሻሩት ለ90 ደቂቃ የዘለቀ ዝርዝር አቤቱታ ካደመጡ በኋላ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፤ ዳኛውን ይህን ውሳኔ እንዲወስኑ ያበቃቸው ምክንያት ግን ይፋ እንዳልተደረገ አስታውቋል።
ቲክቶክ የፍርድ ቤት ውሳኔውን አድንቆ መብቱን ለማስጠበቅ ጥረቱን እንደሚቀጥል ጠቁሞ፤ “ፍርድ ቤቱ ካቀረብናቸው ሕጋዊ መከራከሪያዎች ጋር መስማማቱ አስደስቶናል” ሲልም አቋሙን ይፋ አድርጓል።
ቲክቶክ ከአፕል እና ጎግል ፕለይ ስቶር ላይ መተግበሪያውን ማንሳት ከአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚቃረን ነው ብሎ አጥብቆ ከመከራከሩ ባሻገር፤ ሰዎችም ቲክቶክን እንዳይቀላቀሉ መከልከሉ የሰዎች የመናገር መብት የሚጥስ ነው ሲልም ቅሬታውን አሰምቷል።
ቲክቶክ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጉዳይ አስፈጻሚ ነው ሲሉ የተከራከሩት የአሜሪካ መንግሥት ጠበቆች፤ አሜሪካውያን ቲክ ቶክን እንዳይጠቀሙ የማድረግ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉም ከመግለጽ ባሻገር፤ በቻይናው ኩባንያ ባይቴንዳንስ ባለቤትንት የሚተዳደረው ቲክቶክ ለአሜሪካ ብሔራዊ ስጋት እንደሆነም አስረድተዋል።