ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በቀጣዮቹ ሳምንታት የሚጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር ቅድመ ዝግጅት እያደረግኹ ነው አለ።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኮሚዩኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሐረግ ማሞ ፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሙቀት መለኪያ፣ እና የንጽህና መጠበቂያ በሃገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች፣ መምህራንና በአጠቃላይ የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብና በዓለም ዐቀፍ ደረጃም ሆነ ሃገሪቱ ተቀብላ ተግባራዊ ስታደርጋቸው የነበሩ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችንም በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደ ግዴታ መቀመጡንም ሓላፊዋ ገልጸዋል።
መንግሥት መደበኛ ትምህርትን ከማስጀመር ጋር በተያያዘ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ወላጆችና ተማሪዎችም ራሳቸውን በመጠበቅ ረገድ ተገቢውን ቅድመ መከላከል መተግበር ይኖርባቸዋልም ተብሏል።
ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው መረጃ መሰረት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሕዳር 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ. ም የሚሰጥ ሲሆን ፈተና ላይ መቀመጥ የሚችሉት 7ኛ ክፍልን ተምረው ያጠናቀቁና የ8ኛ ክፍልን የአንደኛ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።
በተያያዘ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መውሰድ የሚችሉት የ11ኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀቁ እና የ12ኛ ክፍልን የመጀመሪያ ሴሚስተር ትምህርት የተከታተሉ ብቻ ናቸው ያለው ትምህርት ሚኒስቴር፤ ከሕዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ይሰጣል ብሏል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሚኒስቴሩ በኦንላይን (በበይነ መረብ) የሚሰጥ ሲሆን፤ በአገሪቷ ካለው የኢንተርኔት ስርጭት ማነስና የአቅርቦቱ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ አሠራሩ ጥያቄ ቢያነሳም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለፈተና መመረጣቸውንና ፤ ከኢንተርኔት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችንም ለመቅረፍ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል።
ይሁን እንጂ በጉዳዮ ላይ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ነገ የሰጡ ተማሪዎችና ወላጆች ፈተናው በኢንተርኔት መሆኑ ለስርቆት ይጋለጣል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። ይህ ሁኔታ ከተከሰተ ደግሞ በቂ ዝግጅት ለፈተናው ያደረጉ ተማሪዎችን ስሜት ይጎዳል ተብሎ ተፈርቷል።