ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ ከ5 ሺኅ 700 በላይ ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በተፈጸሙ ወንጀሎች ዙሪያ ሲያካሂድ የነበረው ምርመራ ማጠናቀቁን ጠቁሞ፤ ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ በ5 ሺኅ 728 ሰዎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ የእርስ በእርስ ግጭት በመቀስቀስ በሚል ወንጀል ክስ መመስረቱን አስታውቋል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ ፤ በተጠርጣሪዎቹ ወንጀል ምርመራ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ተሳታፊ ሆነው መቆየታቸውን ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፍቃዱ ፀጋ አስረድተዋል።
ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል 3 ሺኅ 377 በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ሥር የሚወድቅ እንዲሁም 2 ሺኅ 351 በኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር ክስ የተመሠረተባቸው ሲሆን፤ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች በ114 በኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ደግሞ በ374 የክስ መዛግብት ክሱ መደራጀቱ ተሰምቷል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ምርመራ ተጠናቆ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ክስ መመስረት እንደሚጀመር ሀሙስ እለት መግለጻቸው አይዘነጋም።
በቁጥጥር ሥር ከሚገኙት መካከል ፖለቲከኞች መኖራቸው የገለጹት ጠቅላይ ዐቃቤ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ ፖለቲከኞቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግን በፖለቲካ ተሳትፏቸው አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።
በቀጥጥር ሥር ከዋሉት ከተጠርጣሪዎች ብዛት እና ከወንጀሉ ስፋት አንጻር የምርመራ ጊዜው ረዥም ጊዜ እንደወሰደ የፌደራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ፍቃዱ ጸጋ፤ አነስተኛ የወንጀል ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎችም ጉዳያቸው እየታየ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በዋስትና ይለቀቃሉ ብለዋል።