ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አፍሪካ በህገወጥ መንገድ 836 ቢሊዮን ዶላር ወደ ተለያየ ሃገራት እንደተሸጋገረባት አንድ ሪፖርት ይፋ አደረገ።
በቅርቡ የወጣው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ አፍሪካ ይህንን ያህል መጠን ገንዘብ ያጣችው ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ፣ አልማዝና ፕላቲኒየም የመሳሰሉ ማዕድናት ጋር በተገናኘ ከሌሎች ሃገራት ጋር በምታደርገው የውጪ ንግድ በኩል መሆኑ ተሰምቷል።
ይህ ዝርፊያ የተካሄደው ከሙስና፣ ሌብነትና ግብር ማጭበርበር ጋር የተያያዘ መሆኑም ተነግሯል። ሪፖርቱን ያወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግድና ልማት ((UNCTAD) ሲሆን ፤ የአስራ አምስት ዓመታት መረጃንም ማጠናቀሩን ገልጿል።
አህጉሪቷ ያለባት ብድር 770 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ከሁለት ዓመት በፊት ያለውን መረጃ ዋቢ ያደረገው ሪፖርት አህጉሪቷ ከተሻገረባት መጠንም ጋር ሲወዳደር የዓለም ንፁህ አበዳሪ ያደርጋታል ብሏል።
“እንዲህ ባለ ህገወጥ መንገድ የገንዘብ ዝውውር አህጉሪቷም ሆነ ህዝቧ የወደፊቱን እያጡ ነው። ይህ ሁኔታ ግልፅነት፣ ሓላፊነት የጎደለው ማሳያ ሆኗል፤ አህጉሪቷም ያሏት ተቋማትን እምነት የሸረሸረ ነው” ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ንግድና ልማት ዋና ጸሐፊ ሙኪሳ ኪቱዩ ገልጸዋል።
የገንዘቡ መጠን ከፍተኛ መሆንም የአፍሪካ መንግሥታት በጤና ሥርዓቱ፣ ትምህርትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖም እንደሚያሳርፍ እየተነገረ ነው።
“እንዲህ አይነት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሙስና የአፍሪካ ልማት እክል ሆኗል። በከፍተኛ ሁኔታም አገሪቷ በውጭ ምንዛሬ ድርቅ እንድትመታ ምክንያት ሆኗል። በአገራቱ ውስጥ ያለው የምርት አቅርቦት እንዲያሽቆለቁል ፣ የንግዱና አጠቃላይ ምጣኔ ኃብቱ እንዲጎዳና ድህነትና አለመጣጠን እንዲከፋ አድርጎታል” ሲል ሪፖርቱ የችግሩን ጥልቀት አሳይቷል።