ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በቅርቡ የሚከፈቱትን የትምህርት ቤቶችን ዝግጁነትን የሚያጣራ ኮሚቴ ወደ ሥራ መግባቱን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።
ትምህርት ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር/ ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፤ በተለይ ወላጆች በአብላጫው የሚሳተፉበት ይህ ኮሚቴ ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከአስተዳደር ዘርፍ እንዲሁም ከወላጆች የተውጣጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኮሚቴው በሚቀጥሉት 3 ሳምንታት ውስጥ ትምህርት ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ የሚገመግም፣ ከትምህርት ሚኒስቴር የሚላኩ ቁሳቁሶች መድረሳቸውን የሚያጣራ፣ ሌሎች ድጋፎችን የሚያስተባብር፣ በትምህርት ቤቶች አስፈላጊው ግብዕቶች መኖራቸውን የሚመለከት፣ በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ በአጠቃላይ ትምህርት ማስኬድ የሚችልበት ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ይገመገማል ተብሏል።
የተዋቀረው ኮሚቴ የትምህርት ቤቶችን ነባራዊ ሁኔታ ገምግሞ ውሳኔ ሲያሳልፍ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ሁኔታም የሚወሰነው የትምህርት ቤቶች ተማሪዎቹን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጁነቱ ሲኖር መሆኑም ተሰምቷል።
በግል ትምህርት ቤቶችም የወላጅ ኮሚቴዎች የትምህርት ቤቱን ዝግጁነት ካላረጋገጡ እና ካላመኑበት ትምህርት ቤቱ ትምህርት መጀመር እንደማይችል የትምህርት ሚኒስትሩ ከወዱሁ አስታውቀዋል።