ሥልጠና እንዲወስዱ 5 ኪሎ ካምፓስ ገብተው የነበሩ ዓይነ ስውራን ተማሪዎች በፖሊስ ተባረሩ

ሥልጠና እንዲወስዱ 5 ኪሎ ካምፓስ ገብተው የነበሩ ዓይነ ስውራን ተማሪዎች በፖሊስ ተባረሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በታህሳስ ወር የሚሰጠውን ሃገር ዐቀፍ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና (ማትሪክ) በኦንላይን ስለሚወስዱ አስቀድመው ሥልጠና እንዲያገኙ አዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የገቡ ወጣቶች በድንገት በፖሊስ እንዲባረሩ ተደረገ።

አምና መሰጠት የነበረበት የ12ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ፈተናው በወርሃ ታህሳስ እንደሚሰጥ መግለፁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ ፈተናው በኢንተርኔት የሚሰጥ በመሆኑ ዐይነ ሥውራን ተማሪዎች የኦን ላይን አጠቃቀም  ሥልጠና ከወዲሁ እንዲያገኙ በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ ካምፓስ እንዲገቡና ሥልጠና እንዲጀምሩ ተደርጎ ነበር።
በዚህ መንገድ በሁለት ፈረቃ ሥልጠና ላይ የነበሩ ዐይነ ስውራን ተፈታኖች ቀድሞ የተነገራቸው አምስተኛ ሳምንት ሳይደርስ በድንገት በፖሊስ አማካይነት ግቢውን ለቅቀው እንዲወጡና ወደመጡበት እንዲበተኑ መደረጉን ኢትዮጵያ ነገ ከተማሪዎቹ መገንዘብ ችሏል።
 ዓይነ ስውራኑ ተማሪዎች ለቅድመ ዝግጅት ወይም ሥልጠና አምስት ኪሎ ወደሚገኘው አዲስ አበባ ዮንቨርስቲ እንዲገቡ ሲደረግ ከወቅቱ አንገብጋቢ ችግር አኳያ ትኩረት ተሰጥቷቸው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዳልተደረገላቸው ለኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ የገለፁት  ተማሪዎቹ፤ በሥልጠናው ወቅትም ከንክኪ ፀዳ በሆነ መንገድ ተማሪዎቹ ግንዛቤ እንዲያገኙ አለመደረጉንም ተናግረዋል።
ዓይነ ስውራን ተፈታኝ ተማሪዎቹ ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ዮንቨስርቲው ግቢ እንዲገቡ ቢደረግም፣ አሁን ላይ ምንም ዓይነት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ሳይደረግላቸው ወደየመጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን የጠቆሙ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ተማሪዎች፤ በተለይም አራት ተማሪዎች ኮቪድ 19 ቫይረስ የተያዙ በሚመስል ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ቢታመሙም በዝምታ መታለፋቸው በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ይፋ አድርገዋል።
ከሥልጠናው በኋላ ለዓይነ ስውራኑ ተማሪዎች አንድ አንድ ላፕቶፕ በነፍስ ወከፍ እንደሚሰጣቸው ትምህርት ሚኒስቴር ቀደም ሲል አስታውቆ የነበረ ቢሆንም አሁን በግልፅ እንደታየው ለተማሪዎቹ የተገባው ቃል ሳይፈፀም በባዶ መሸኘታቸውን ለማወቅ ችለናል።

LEAVE A REPLY