ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ለሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ተብሎ ከ9 መቶ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርገው የተገዙለትን ታብሌቶች ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሰጥቼያለሁ አለ።
ባለፈው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ለነበረው የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ አገልግሎት ተገዝተው የነበሩት ታብሌቶች 180,000 እንደነበሩ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ ገልጸዋል።
ታብሌቶቹ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተከፋፈሉ ያለው ሀገር ዐቀፍ የህዝብ እና የቤቶች ቆጠራው በመራዘሙ ምክንያት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
እነዚህ ከ900 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣባቸው መሳሪያዎች በሁለተኛ ደረጃ ከጊዜ ብዛት እንዳይበላሹ ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል መባሉን ሰምተናል።
የታብሌቶቹ ግዢ በወቅቱ ከሀገረ ቻይና እንደተፈፀመ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አቅራቢዎቹም ሁዋዌይ እና ሌኔቮ የተባሉ የቻይና ኩባንያዎች እንደሆኑም አብራርተዋል።
ከተገዙ 3 ዓመት የሞላቸው ታብሌቶች ከተሰጧቸው መንግሥታዊ መስሪያ ቤቶች ውስጥ አንዱ ግብርና ሚኒስቴር ሲሆን፤ የግብርና ሚኒስቴርም ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ 35 ሺኅ 410 ታብሌቶችን መረከቡን አረጋግጧል።