ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በርካታ ዘመናት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሠፊ ድርሻ የነበራቸው፣ የአደባባይ ምሁሩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ትናንት ለሊት በ90 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
የጂኦግራፊ መምህር፣ፖለቲከኛ፣ደራሲ፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው በርካታ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ለሀዘን ዳርጓል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዕድሜያቸውን ሙሉ ለኢትዮጵያ ይበጃል ያሉትን ሁሉ ፊት ለፊት ከመናገር የማይቦዝኑ ከመሆናቸው ባሻገር በፖለቲካ አመለካከታቸውም ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ለእስር መዳረጋቸው አይዘነጋም።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት፤በተመራማሪነት ያገለገሉ ከመሆናቸው ባሻገር፤በውጪ ሃገር የተለያዮ ዩኒቨርስቲዎችም አስተምረዋል፡፡
በጊምቢ አውራጃ አስተዳዳሪነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ መስርተውና መርተው የህዝባቸውን የሰብአዊ መብት እንዲከበር ለማድረግ በእጅጉ ደክመዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ በመገናኛ ብዙሃን ስለሃገራቸው እድገትና ስለህዝባቸው ደህንነት አስተያየት ከመጻፍ ያላቋረጡ ምሁር ሲሆኑ፤ በቅርቡ ለሕዝብ ሊያደርሱት የነበረ መጽሐፍ ማተሚያ ቤት አስገብተው ነበር። በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ነገ በአደባባይ ምሁሩ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸው ወዳጅና ዘመዶቻቸው፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን መፅናናትን ይመኛል።