ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መስከረም 23 እና 24 ለሚከበረው የእሬቻ በዓል ከኦሮሚያ የተለያዮ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የተንቀሳቀሱ መንገደኞች ወደ ከተማው እንዳይገቡና ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተናገሩ።
በተለይም ቅዳሜ መስከረም 23 ቀን በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረው ብቸኛዋ የዋዜማ በዓል ወይም ሆራ ፊንፊኔን ለማክበር በገፍ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሞከሩ በርካታ ቄሮዎች በፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል።
ከሸኖ ከተማ በተነሳ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪ ለሸገር እንደተናገሩት ከሆነ የእሬቻ በዓልን ለማክበር ነው የምትጓዙት በሚል አዲስ አበባ መግቢያ ላይ እርሳቸው የተሳፈሩበትን መኪና ጨምሮ፤ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች እየተለዮ ከነጫኑት ተሳፋሪ ወደመነሻቸው እንዲመለሱ መደረጉን ለሸገር ራዲዮ ገልጸዋል።
የፀጥታ አካላት ከቤት መኪኖች ውጪ የትኛውንም አይነት የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች እንደማያመላልሱ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች በርካታ ሰዎች ለሕክምና፣ ለሥራና ለፍርድ ቤት ቀጠሮን ጨምሮ ለተለያየ ጉዳይ የሚመጡ መንገደኞችም በእሬቻ ሰበብ ወደአዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከላቸውን አስረድተዋል።
ጉዳዮን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ሓላፊ ጌታቸው ባልቻ፤ የፀጥታ ሓይሎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ እየከለከሉ ያሉት ሕዝብን ከሕዝብ ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ መፈክሮችንና ባነሮችን የያዙ፣ የተለያዮ ድርጅቶችን ወይም ፓርቲዎችን ባንዲራ ይዘው የተገኙ ብቻ ናቸው ሲሉ ተከራክረዋል።