ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሽብርተኝነት የተጠረጠሩት እነ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ለአልጀዚራ እኛን በተመለከተ ጽንፈኞች በማለት የተናገሩት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉን ፍርድ ቤቱ ጠርቶ እንዲጠይቅላቸው አቤቱታ አሰሙ።
አቶ በቀለ ገርባና ጀዋር መሐመድ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በመገኘት ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ ነጻ ሆኖ የመታየት መብታቸውን የሚጻረር መሆኑን፣ ለህይወታቸው እንደሚያሰጋቸውም ገልጸዋል።
“በእኛ ክስ ላይ ምስክሮች እንኳ ሳይሰሙ፣ የፖለቲካ ባለስልጣናት፣ በተለይም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤቱ እኛ ላይ ውሳኔ እንዳስተላለፈ አድርገው ነበር የተናገሩት” ያለው ጃዋር መሐመድ፤ ጽንፈኞች ተብለናል፤ እንዲሁም ግርግር እንደፈጠርን እና ሰው እንደገደልን ወስነዋል ሲልም በቅርቡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲጠየቁለት አቤቱታቸውን አቅርቧል።
“ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ እኛ መከላከል በማንችልበት ሁኔታ ለውጪ አገር ሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተዋል። ይህም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለልተኛ መሆንን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው” ያሉት አቶ በቀለ ገርባም ተመሳሳይ አቤቱታ አሰምተዋል።
ጉዳዮን የመረመረው ፍርድ ቤቱም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሚቀጥለው ቀጠሮ ላይ በጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ዛሬ የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በ24 ሰዎች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የከፈተውን ክስ ለተከሳሾች አሰምቷል። ፍርድ ቤቱ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 15 ድረስ ያሉ ተከሳሾችን ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ ሁከት በመፍጠር በአዲስ አበባ ከተማ የ13፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ 167 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ 360 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እና 4.6 ቢሊዮን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም በዝርዝር አቅርቧል።
በተጨማሪም ያለፈቃድ የጦር መሳሪያዎችን ይዘው በመገኘትና የቴሌኮም ማጭበርበርን መፈፀም የሚሉ ጉዳዮች ክሱ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን፤ 18ኛ ፣ 21ኛ፣ 6ኛ፣ 8ኛ፣ 9ኛ፣20፣7ኛ ተከሳሾች አማርኛ የማይሰሙ መሆናቸው ተገልጾ እነርሱ ላይ የቀረበውን ክስ አለመረዳታቸውን ተከትሎ፣ ጠበቆቻቸው በደንበኞቻቸው ላይ የተከፈተውን ክስ ማረሚያ ቤት በመገኘት ማሳወቅ እንደሚችሉ መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል።