ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በወ/ት ብርቱኳን ሚዴቅሳ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ እንደሚገኝና ለምርጫውም 50 ሚሊዮን ሰዎች ለመራጭነት ሊመዘገቡ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል።
ሥድሥተኛውን ሃገር ዐቀፍ ምርጫን አስመልክቶ እያደረጋቸው ያሉ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ሥራን አስመልክቶ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ይፋዊ መግለጫ ሰጥቷል።
እድሜያቸው ለመምረጥ ደርሶ በምርጫው ይሳተፋሉ ተብለው የሚጠበቁ ሰዎች ቁጥር ከሃገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ወደ ግማሽ ይጠጋሉ ያለው ቦርዱ፤ በመላው ሃገሪቱ በምርጫው ድምጽ የሚሰጡባቸው 50 ሺኅ 900 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩም ከወዲሁ አስታውቋል።
ከድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባን የሚያከናውኑ 152 ሺኅ 700 ሰዎችን ፣ እንዲሁም ለድምጽ መስጫ ቀን 254 ሺኅ 500 ምርጫ አስፈጻሚዎችን እንደሚያሠማራ የገለጸው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በዚህ ዓመት ሊካሄድ እንደሚችል ለሚነገርለት ሃገራዊ ምርጫ በአምስት ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመራጮች መዝገቦች መዘጋጀታቱንም ገልጿል።
የምርጫውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ መራጮች የሚወስዱት ለማባዛት እና አስመስሎ ለማተም የማይቻል፣ የደኅንነት መጠበቂያ ያለው የመራጮች መታወቂያ ካርድ መዘጋጀቱን ከጋዜጣዊ መግለጫው መረዳት ችለናል።
ከዚህ በተጨማሪ ምርጫ ቦርድ እንደ ድምጽ መስጫ ሳጥኖች፣ የሚስጥር ድምጽ መስጫ መከለያዎች፣ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች የያዙ ቦርሳዎች፣ የጠረጴዛ ባትሪ የመሳሰሉ ለምርጫው የሚውሉ ቁሳቁሶችን አዘጋጅቶ መጨረሱንም አረጋግጧል።
ሃገራዊው ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ የሚያመለክተው የጊዜ ሰሌዳ ያልወጣ ቢሆንም፤ ቦርዱ ከወዲሁ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቅልኝ ብሏል።