ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በቦሌ ክፍለ ከተማ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካን ዶላር ከነተጠርጣሪው ይዞ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።
በተጠቀሰው ክ/ከተማ ወረዳ 7 ጉርድ ሾላ ሰፈረ ገነት ተብሎ በሚጠራው ፣ የዉጪ ሃገር ዜግነት ያለው ግለሰብ ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ውስጥ ሃሰተኛ ዶላር እንደሚያዘጋጅ ጥቆማ የደረሰው ከኅብረተሰቡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንደተናገሩት፤ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ2 ሚሊዮን 470 ሺኅ በላይ የአሜሪካን ዶላር ተይዟል።
በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ዛሜሌክስ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢም የውጪ ሃገር ዜግነት ያለው ግለሰብ “ከአንድ የአፍሪካ ሃገር ወደ ኢትዮጵያ በዲፕሎማቶች አማካይነት የሚገባ 5 ሚሊዮን ዶላር አለ” በማለት ሌላ ግለሰብን በማታለል ገንዘብ ለመውሰድ ሲሞክር ለሊያዝ ችሏል።
ነገሩ ያልጣማቸው የግል ተበዳይ ተጠራጥረው ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎችን፣ እንዲሁም በገንዘብ መጠን የተቆራረጠ ወረቀት በኤግዚቢትነት ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ጠቁሟል።
በሌላ በኩል ከህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን ባከናወነው የክትትል እና ቁጥጥር ተግባር 7ሚሊዮን 243 ሺኅ 385 የኢትዮጵያ ብር መያዙን ይፋ አድርጓል።
ለህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ የተዘጋጁ 117 ሺኅ 703 የአሜሪካን ዶላር፣ 400 ዩሮ፣ 740 የእንግሊዝ ፓውንድ፣ 700 የደቡብ አፍሪካ ራንድ፣ 8ሺኅ 50 የአረብ ኤምሬትስ እና የሌሎች የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በአጠቃላይ ከህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ እና የብር ኖት ቅያሪ ጋር ተያይዞ ከ15 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ሥር እንደዋለ በመነገር ላይ ነው።