ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አነጋጋሪ በሆነው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ አስቀድመው ለተወሰደባቸው መሬት ካሳ የተከፈላቸው አርሶ አደሮች በተጨማሪ ቤት እንዲወስዱ መደረጋቸው በእጅጉ አነጋጋሪ ሆኗል።
በወያኔ ዘመን ለኮንዶሚኒየም ግንባታ በሚል አርሶ አደሮቹ መሬታቸው ቢወሰድባቸውም በሰዐቱ በቂ ይሁንም አይሁን አስፈላጊው ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ይታወሳል። በርካታ አርሶ አደሮች ቦታውን ከነበራቸው የሰፈራ ይዞታ ውጪ በተስፋፋፊነት ለዓመታት መሬታቸውን ያደላደሉ መሆኑ ሲታወስ ደግሞ በህወሓት መራሹ መንግሥት ገንዘብ እንዲከፈላቸው መደረጉ እድለኛነታቸውን ያሳያል የሚሉ ወገኖች በርካቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ ከለውጡ ማግስት አንስቶ በታከለ ኡማና በአዳነች አቤቤ መስተዳደር በግልፅ በሚተገበረው የፊንፊኔ ኬኛ ፖለቲካ አማካይነት፣ አዲስ አበቤ ከእለት ጉርሱ እየቀነሰ ለኮንዶሚኒየም ቢከፍልም አርሶ አደሮቹ በጊዜው ተገቢውን ክፍያ አላገኙም በሚል የመኖሪያ ቤቱ እየተሰጣቸው ይገኛል።
ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግቢ ውስጥ በተካሄደው ርክክብ ላይ አዳነች አቤቤ ለ100 ሰዎች ቁልፍና የቤት ካርታ ያስረከቡ መሆኑን ያመላከተው መረጃ፤ 51 ሺኅ 229 ዕጣ የወጣላቸው እድለኞች እና 22 ሺኅ 915 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ናቸው የርክክብ ስነ ስርዓቱ እንደተጀመረላቸው አውጇል።
የቤት እድለኞች እና የልማት ተነሺ አርሶ አደሮቹ የሚደረገው የቁልፍ፣የካርታ እና የውል ርክክብ እስከ ጥቅምት 12 ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፣ በ13ኛ ዙር ዕጣ ወጣላቸው የ20/80 ባለዕድለኞ ብዛት 32 ሺኅ 253 ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 7 ሺኅ ያህሉ ውል እንደጨረሱና 245ቱ ደግሞ ቁልፋቸውን እንደተረከቡ ተነግሯል።
በ40/60 መርሃግብር ዕጣ የወጣላቸው ብዛት 18,576 ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 17 ሺኅ 256ቱ ውላቸውን እንደጨረሱ፣ ከነዚህ ውስጥም 14 ሺኅ 296ቱ ቁልፍ ተረክበው፣ ቀሪዎቹ በሂደት ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በመጀመሪያ ዙር ዕጣ የወጣላቸው 22 ሺኅ 915 ሲሆኑ፤ በዛሬ ዕለት የቁልፍና ካርታ ማስረከብ ሂደቱን ጀምረዋል። ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ቤት ለተፈናቃይ አርሶ አደሮች በሚል መከፋፈሉ፣ በሁለተኛው ዙር እደላም ቀሪ አርሶ አደሮችን በልማት ተነሺ ስም የቤት ባለቤት ለማድረግ መታቀዱ ፣ “ይሄ የተረኝነት ፖለቲካ መች ይሆን የሚቆመው?” የሚል ጥያቄን በአዲስ አበባ ዘንድ ፈጥሯል።