ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ህወሓት በተለያዩ የፌደራል መንግሥት የፖለቲካ ሹመት ቦታ ላይ የነበሩ አባላቱ፣ የክልሉ ተወካይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ሓላፊነታቸውን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ።
ከፌደራል መንግሥቱ ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ ያፈነገጠውና ጳጉሜ 4 ቀን እውቅና ያልተሰጠው ክልላዊ ምርጫ ያካሄደው ህወሓት እንዲህ ዓይነት ትእዛዝ ለአባላቱ እንዳስተላለፈ የገጹት ጌታቸው ረዳ፤ የፓርላማው የስልጣን ዘመን በትናንትናው ዕለት ማክተሙን ጠቁመው፣ ከፓርላማው በተጨማሪ ፓርላማው ያቋቋመው መንግሥትም፣ ሆነ ካቢኔው የተመረጡት ለአምስት ዓመት ስለነበር የሥልጣን ዘመናቸውን አጠናቀዋል ብለዋል።
ይህን ተከትሎ ዛሬ በተከፈተው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ የፓርላማ ዘመን 6ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ትግራይ ክልል ተወካዮቹን እንደማይሳተፍ አሰቀድመው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“የትግራይ ክልል ተወካዮች ከምክር ቤቱ እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። በፓርላማ ብቻ ሳይሆን በካቢኔ ውስጥ፣ በሌሎች የመንግሥት የፖለቲካ ሹመት ቦታዎች ላይ የነበሩ የህወሓት ተወካዮችም እንደዚሁ እንዲወጡ ተደርገዋል” ያሉት የህወሓት ቃል ዐቀባይ፤ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም ሲሉ አጣጥለውታል
በአሁኑ ሰዐት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ካቢኔያቸው፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ምንም አይነት ሕጋዊ ሥልጣን የላቸውም የሚሉት ጌታቸው ረዳ፤ ከዛሬ ጀምሮ ከእነዚህ አካላት ጋር ምንም አይነት ሕጋዊ ግንኙነት ይኖራል ብለን አናስብም ሲሉም የድርጅታቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል።