ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተጠሩት የእግር ኳስ ቡድን አባላት መካከል አምስቱ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተሰማ።
ለቀጣዮ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የአፍሪካና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በቅርቡ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሆነው በተሾሙት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የተጠሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት ዝግጅት ወደሚያደርጉበት ትናንት ማምሻውን ገርጂ አካባቢ የሚገኘው ካፍ አካዳሚ ገብተዋል።
ወደ ካምፕ የገቡት ተጫዋቾች ትናንት ማምሻውን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ያደረጉ ሲሆን፣ ከ36 የቡድኑ አባላት መካከል አምስቱ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው አሁን ላይ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ቫይረሱ የተገኘባቸው አምስቱም ራሳቸውን አግልለው ክትትል እየተደረገላቸው ነው። ከምርመራው በኋላ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠው 31 የቡድኑ አባላት ዝግጅት ወደሚያደርጉበት የካፍ አካዳሚ ገብተዋል።
ከኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ ጋር ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈው አሰልጣኝ ውበቱን ጨምሮ በሦስት አሰልጣኞች ለማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት የጀመረው፤ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ዛሬ ጀምረዋል።