ስምንት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባሕር ላይ ሲሞቱ፣ 12ቱ ደብዛቸው ጠፍቷል

ስምንት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባሕር ላይ ሲሞቱ፣ 12ቱ ደብዛቸው ጠፍቷል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ጭናለች የተባለች ጀልባ በባህር ላይ አደጋ ደርሶባት ስምንቱ ሕይወታቸው በርካቶች እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁንና ደብዛቸው መጥፋቱ ተሰማ።

 በጅቡቲ ባሕር ዳርቻ አቅራቢያ አደጋው በደረሰባት ጀልባ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ከመካከላቸውም ስምንት ስደተኞች ሲሞቱ 12 ሰዎች ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም ብሏል።
በባሕር ላይ በደረሰው አደጋ ለሞት ከተዳረጉትና የደረሱበት ሳይታወቅ ከቀሩት ውጪ የ14 ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ የተቻለ ሲሆን፣ ሌሎቹንም ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።
እንደ መረጃው ከሆነ ለስደተኞቹ ሞት ምክንያት የሆነቸው ጀልባ ሰዎቹን አሳፍራ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት በግድ እንድትንቀሳቀስ ከተደረገች በኋላ ነው አደጋው የተከሰተው።
አደጋው የገጠማት ጀልባ ከሰላሳ በላይ ሰዎችን አሳፍራ የነበረ  ሲሆን ፤ በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት ስደተኞች መካከልም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ ተብሎ እንደሚገመት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞቹ ድርጅት ይፋ አድርጓል።
በደረሰው አደጋ ለሞት የተዳረጉትና የደረሱበት ያልታወቁት እነዚህ ስደተኞች ከየመን ወደ ጅቡቲ እየተመለሱ የነበሩ ናቸው። የአካባቢው ሃገራት በሁለት ጎራ ተከፍለው በሚደግፉት ለዓመታት በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው የመን ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ለከባድ ችግር ተጋልጠዋል እየተባለ ነው።
በባሕር ላይ ሳሉ በጀልባቸው ላይ አደጋ የደረሰባቸው ስደተኞችም የመን ውስጥ ካለው ጦርነት ለመሸሽ ወደ ጂቡቲ እየተመለሱ ያሉ ስደተኞች ሳይሆኑ እንደማይቀር መገመቱን የጠቆመው ድርጅቱ፤ ሳዑዲ አረቢያ የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር በሚል ከ14 ሺኅ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ከአገሯ ማስወጣቷንና  እነዚህም ስደተኞች በየመን መንቀሳቀሻ አጥተዋል ብሏል።

LEAVE A REPLY