ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዘንድሮ ይካሄዳል የተባለው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የበርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ በፍትሀዊነት የሚሰማበት እንደሚሆን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ።
ዛሬ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነሥርዓት ሲያካሂዱ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ የተካሄዱት ምርጫዎች ከተሳትፎና ፉክክር አንጻር ጉልህ ችግሮች ነበሩባቸው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ያለፈው ዓመት ሃገሪቱ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት ቢሆንም በበርካታ ውጣ ውረዶች ማለፏን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም እንዲሰፍን ላደረጉት ጥረት፣ በተለይም ከኤርትራ ጋር የነበውን አለመግባባት ለመፍታት የሄዱበት ርቀት እውቅና ያገኘበትና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የሆኑበት አመት እንደነበር የተናገሩት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ዓመቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተመለከተ የነበሩትን የአሠራር ችግሮች በማጥናትና መፍትኄ በመስጠት የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የተከናወነበት መሆኑንም ገልፀዋል።
በተያዘው ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት የሚጀምርበት እንደሚሆንም ያበሰሩት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤
ያለፈው ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጭነት ከቢሮ እስከ ሃገር በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ሸገርን የማስዋብ ሥራ በተያዘለት እቅድና በተቀመጠለት ጊዜ መከናወኑ አቅደን መስራት እንደምንችል ያሳየንበት ነውም ሲሉ የመንግሥታቸውን ስኬታማነት ይፋ አድርገዋል።
ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር አኳያ በተሠራው ሥራ ለ3 ሚሊየን ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ያሉት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ሃገሪቱን በቴክኖሎጂ ለማዘመን በተሠራው ሥራ ሳተላይት እስከማምጠቅ የተደረሰበት ነውም ብለዋል።
ኮሮናን አስቀድሞ ከመከላከል አንጻር በርካታ ሥራዎች ከመሠራታቸውም በላይ ከራሳችን አልፈን ለበርካታ የአፍሪካ ሃገራት የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶችን ያሰራጨንበት አመት ነው ያሉት የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት፤ በኩታ ገጠም እርሻ ለግብርናችን እድገት ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡንና በበጀት አመቱ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው እቅድ በስኬት ተጠናቋል ሲሉ ብልፅግና ፓርቲና መንግሥታቸው ያለፈውን አመት በስኬት ማጠናቀቁን ለማሳየት ሞክረዋል።