ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አርቲስት ሃጫሉን በመግደል ወንጀል የተከሰሱት 4 ግለሰቦች ዛሬ ክሳቸው ተነበበላቸው።
እነዚህ ተከሳሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገ መንግሥትና የጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በቀጠሮዋቸው መሠረት ቀርበው ነው ክሳቸው የተነበበላቸው።
ተከሳሾቹም በቅደም ተከተል ጥላሁን ያሚ ባልቻ፣ ከበደ ገመቹ መገርሳ፣ አብዲ አለማሁ እና ላምሮት ከማል በመባል ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ያለውን ይዘዋል።
ተከሳሾች ለዛሬ ከባለሙያ ጋር ተማክረው ክሱን ለማንበብ በተሰጠው ቀጠሮ መሰረት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተከሳሾች ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌላቸው ሲናገሩ፤ 4ኛ ተከሳሽ የሆነችው ላምሮት ከማል ጠበቃ የማቆም አቅም ቢኖራትም የሚቆምልኝ ጠበቃ አጥቻለሁ ስትል ለፍርድ ቤቱ ገልጻለች።
ተከሳሾች ያቀረቡትን ትዕዛዝ ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የመንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ ከመስጠቱ ባሻገር፣ ተከሳሾቹ በተነበበላቸው ክስ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ለመመልከት ለጥቅምት 4 ቀን 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።