ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነውን ህገ ወጥ የመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ በማስረጃ ያጋለጠው ኢዜማ ሀገሪቱን በተሳሳተ መንገድ ለመበጥበጥ እየጣሩ ባሉ ኃይሎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል አለ።
በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትኅ (ኢዜማ) ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም እያሉ ቅስቀሳ የሚያደርጉ አካላት ላይ መንግሥት ተገቢውን የሕግ እርምጃ እንዲወሰድ በይፋ ጥያቄ አቅርቧል።
“ከመስከረም 25 / 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፣ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም” በማለት ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትን መንግሥት በንቃት እየተከታተለ፣ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ኢዜማ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ መንግሥትን አሳስቧል።