ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሤ ህወሓት ያቀረበውን ሥልጣን የመልቀቅ ሀሳብ እንደማይቀበሉ ገለፁ

ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሤ ህወሓት ያቀረበውን ሥልጣን የመልቀቅ ሀሳብ እንደማይቀበሉ ገለፁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ህወሓት በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ያላቸውን ሥልጣን እንዲለቁ አስቸኳይ መመሪያ ካቀረበላቸው አባላቶቹ መሀል አንዷ የሆኑት የህዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ተሳታፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሤ  ይህንን ሀሳብ እንደማይቀበሉ ተናገሩ።

የፌዴራል መንግሥቱ ሕገ መንግሥቱን ጥሷል ያለው ህወሓት በፌደራል ደረጃ ምርጫን በማሸነፍ በሚያዙ ኃላፊነቶችና ውክልና የነበራቸው የህወሓት አመራሮችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን በመተው ወደ ድርጅታችሁ ህወሓት ጽ/ቤት ሪፖርት እንድታደርጉ ሲል ማዘዙ ይታወሳል።
በትዕዛዙ መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ፣ የህዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ሮማን ገ/ሥላሴ ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አልማዝ መኮንን ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ገ/እግዚአብሔር ፣ አምባሳደር ዓባይ ወልዱን እና አዲስ ዓለም ባሌማን ጨምሮ 13 አመራሮች ለህወሓት ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡
ጦርነት ናፋቂው ህወሓት ከዚህ በተጨማሪም የህወሓት አባል የሆኑ 27 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ከዚህ በኋላ በፓርላማው ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳያደርጉም አዟል።
ህወሓት ይህንን ውሳኔውን በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ሲያስነብብ በአምስተኛ ተራ ቁጥር ላይ ያስቀመጣቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ሮማን ገ/ሥላሴ ጉዳዩን እንዳልሰሙትና ትእዛዙንም እንዳላነበቡት ገልጸዋል።
“እኔ የምሰራው ህዳሴው ግድብ ላይ ነው፣ ግድቡ ደግሞ የሁሉም ብሔር ፣ የሁሉም ሕዝብ ሀብት ነው” ሲሉ ጉዳዮን አስመልክቶ ለአል ዐይን ምላሽ የሰጡት ወ/ሮ ሮማን ጥሪውን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠየቁም ቁርጥ ያለ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ትናንትና በተከናወነው በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ የተገኙት ብቸኛዋ የትግራይ ሕዝብ ተወካይ ወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ፤ ህወሓት ከአባልነታቸው ተነስተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ከጻፈላቸው የፓርቲው አባላት መካከል ቢሆኑም ፣ የሕዝብን ድምፅ በማክበር ወደ ስብሰባው መምጣታቸውን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲናገሩ በግልጽ ታይተዋል።
“የተለያየ ፓርቲ ወክለን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብንገባም ምክር ቤት ስንገባ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወኪል ነን” ያሉት ወ/ሮ ያየ፤ አንድ የምክር ቤት አባል ከአባልነቱ የሚነሳው የወከለው ህዝብ አይወክሉኝም ሲል አሊያም የሥራ ዘመን ሲያበቃ እንደሆነም ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY