የታላቁ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፀመ

የታላቁ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፀመ

 ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአንጋፋው ፖለቲከኛና የአደባባይ ምሁር የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስርዓተ ቀብር በቅድስት ሥላሤ ካቴድራል ዛሬ ተፈፀመ።
ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ ከተማ በተከበሩት የእሬቻ በዓሎችና በወቅቱ ይነሳል ተብሎ ተገምቶ ከነበረው የፀጥታ ችግር አኳያ እሁድ ዕለት ሊከናወን የነበረው ሥርዓተ ቀብራቸው እስከ ዛሬ ድረስ ሊጓተት መቻሉን ኢትዮጵያ ነገ ከቅርብ ሰዎቻቸው መረዳት ተችሏል።
በሥርዓተ ቀብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሓላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው መገኘታቸው ታውቋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ሰብኣዊ መብቶች መከበር ባደረጉት ትግልም የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
በአካዳሚክ እውቀታቸውም በድርቅና ረሃብ፣ በማኅበራዊና ሌሎች መስኮች ጥናትና ምርምሮችን ያደረጉ ሲሆ፤ በምርጫ 97 ወቅት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በቀጣይ የማይደገም የሚመስል ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነትን ከዳር እስከ ዳር ያገኘው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ እንዲመሠረትም ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም በ91 ዓመታቸው አርፈው፤
ሥርዓተ ቀብራቸው በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

LEAVE A REPLY