ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ቢሾፍቱ ከተማ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ቀደም ሲል ተፈቅዶላቸው የነበረው የመቶ ሺኅ ብር ዋስትና እንዲፀና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ዛሬ መወሰኑ ተሰማ።
ልደቱ አያሌው ዳግም በዋስ የመውጣት መብት ያላቸው መሆኑን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያረጋገጠ ቢሆንም እስከ ቀኑ 11 ሰዐት ድረስ ልደቱ አያሌው አለመለቀቃቸውንና በእስር ላይ እንደሆኑ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር (ኢዴፓ) አቶ አዳነ ይፋ አድርገዋል።
ዛሬ መስከረም 26፣ 2013 ዓ.ም የዋለው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት የዋስትና እግድን በተመለከተ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ሲሆን፣ “የአቶ ልደቱ የዋስትና ጥያቄ እግድ አይገባውም፣ ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል” የሚለውን የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመቶ ሺኅ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ሲል ያሳለፈውን ውሳኔ አፅንቶ ግለሰቡ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቶ ልደቱ ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከራከሩና፣ የዋስ መብታቸው እንዲከበር የምስራቅ ሸዋ ፍርድ ቤት መወሰኑን ተከትሎ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ፤ አቶ ልደቱ በአደራ ነው ያሉት በማለት አልለቅም ማለቱን በዛሬው ችሎት ላይ ያስታወሱት ተከሳሽ ፤ አሁንም ከትእዛዙ በኋላ እንዲህ አይነት ነገር ሊገጥማቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
” ፖሊስ አልለቅም ሊል ይችላል፤ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ከዚሁ በነፃ ያሰናብተኝ” የሚል ጥያቄ አቶ ልደቱ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ለፖሊስ የአስቸኳይ ትዕዛዝ ከመስጠቱ ባሻገር ፤ የ100 ሺኅ ብር ዋስትናውን ለወሰነው ለምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ትዕዛዙ እንዲደርስ መመሪያ ሰጥቷል።