ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በፓርላማ የፀደቀው አዲሱ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን በሥራ ላይ ለማዋል ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ተሰማ።
በአፍሪካ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ያላቸው ሰዎች የሚያሳውቁበት ወይንም ለሕጋዊ አካላት የሚያስረክቡበት ወርን ተንተርሶ የሰላም ሚኒስቴርና ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በቅርብ በምክር ቤቱ የፀደቀው የጦር መሳሪያ ቁጥጥርና አስተዳደር ተግባራዊ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሕገወጥ የጦር መሳሪያ በመቆጣጠር፣ እንዲሁም ሰላም ለማስፈን ኅብረተሰቡን እና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት የሰላም ሚኒስትሯ ሞፈሪያት ካሚል፤
እስካሁን ባለው አሠራር የሕገወጥ መሳሪያ ዝውውርን መቆጣጣር ያለባቸው ተቋማት የሚፈለገው የቴክኖሎጂ እገዛ እንደሌላቸውም ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በፌደራል ደረጃ ያሉ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በቅርብም ምዝገባ የሚጀመር መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ስልጠናውን በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች ላሉ ባለሙያዎች በመስጠት አዋጁን በሃገር ዐቀፍ ደረጃ ሥራ ላይ ለማዋል ይሠራል ብለዋል።
አሁን ላይ የሚታየው የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚቀጥል ከሆነ ሰላም ጠፍቶ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ኅብረተሰቡም ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል።
መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት በታሕሳስ 2012 ዓ.ም የጦር መሳሪያ አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012 እንዲወጣ መደረጉን ያብራሩት የሰላም ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ሚናስ ፍሰሀ፤ ይህንንም አዋጅ ወደ ተግባር ለመቀየር ደንቦችና መመሪያዎች ተዘጋጅተው መጠናቀቁንም አረጋግጠዋል።
የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታና ሓላፊነት ያለበት መንግሥት እንደሆነ ያስረዱት አቶ ሚናስ፤ ሆኖም ዜጎች ባላቸው የማኀበራዊና ባህላዊ እሴቶች፣ ለደህንነታቸው እንዲሁም በሥራቸው ምክንያት ጦር መሳሪያ እንዲይዙ የሚገደዱበት ሁኔታ ካለ በአዋጁ የወጣውን መስፈርት አሟልተው ሔጋዊ መሆን ይችላሉ ብለዋል።