ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአቶ ልደቱ አያሌው የመቶ ሺህ ብር የዋስትና መብት እንዲጸና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ያስተላለፈውን ማዘዣ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አልቀበልም አለ።
ይህንን የፖሊስ ጣቢያውን እምቢኝነት ተከትሎ እስረኛው ልደቱ አያሌው ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደማያደርጉና መጨረሻውን ዝም ብለው እንደሚመለከቱ አስታወቁ።
ትናንት የተሰየመው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት አቶ ልደቱ አያሌው በመቶ ሺኅ ብር ዋስትና እንዲወጡ የታችኛው ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ማፅናቱን ተከትሎ፣ ጠበቃው የዋስትና መብት እንዲከበር ማዘዣውን ለቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ቢሰጡም፤ ፖሊስ አቶ ልደቱን አልለቅም ማለቱን የኢትዮጵያውያን የኢዴፓ ፕሬዘዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ተናግረዋል።
“ፖሊስ ልደቱን አልለቅም በማለቱ ተስፋ ቆርጠን ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል። አቶ ልደቱ ምንም እንዳይደረግ ብሎ በመከልከሉ፣ እኛም ጠበቆቹም ከዚህ በኋላ በፍትሕ ሥርዓቱ በኩል ተጨማሪ እንቅስቃሴ አናደርግም። እርሱም (ልደቱ) ከልክሎናል፣ እኛም አናምንበትም” ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር ያለውን ሁኔታ ገሀድ አውጥተዋል።
የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመከበሩን ተከትሎ፣ አቶ ልደቱ በፍትኅ ሥርዓቱ ተስፋ እንደቆረጡ የጠቆሙት አቶ አዳነ፤ “ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ከመጠበቅ ውጪ የትም አትሂዱ ብሎናል” ሲሉ የእስረኛው ፖለቲከኛን አቋም ገልጸዋል።
የፍርድ ቤት ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል እየተሻረ እያዩ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ልደቱ አያሌው፣ ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት አቅም አለው ብለን አንሄድም፣ ግን የፍርድ ሂደቱን በፈለጉት መንገድ ያስኬዱታል። የፖለቲካ ውሳኔ ነው ሲሉም በሚያዮት ነገር ተስፋ መቁረጣቸውን አስረድተዋል።
ስለጉዳዩ ትላንት ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እንዳደረጉ የገለጹት የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ አዳነ የኢትዮጵያዊ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ስለሁኔታው ከፖሊስ ጋር እንደሚነጋገሩ እንደገለጹላቸውም ለቢቢሲ ተናግረዋል።