በ1 ዓመት በዓለም ዐቀፍ ተቋማት መቀጠር ከቻሉት 4ሺኅ 500 ኢትዮጵያውያን ባህረኞች መሀል...

በ1 ዓመት በዓለም ዐቀፍ ተቋማት መቀጠር ከቻሉት 4ሺኅ 500 ኢትዮጵያውያን ባህረኞች መሀል በርካቶቹ ኮበለሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና ||  ባህረኞችን አሰልጥኖ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በማስቀጠር በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት ተርታ መሰለፍ የቻለው የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን የባህረኞች መኮብለል እያሳሰበው መሆኑን አስታወቀ።

በአንድ ዓመት ውስጥ ከ7 ሺኀ በላይ ባህረኞችን አሰልጥኖ 4 ሺህ 500 ያህሉን በዓለም ዐቀፍ ተቋማት ማስቀጠር እንደቻለ የገለጸው ባለሥልጣኑ ፤ ባህረኞቹ ወደ አሜሪካና ሌሎች ሀገራት ሲደርሱ እየጠፉ መቸገሩን ይፋ አድርጓል።
ይህ ሁኔታ ባህረኛውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን የተናገሩት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን፤ ተቋሙ በ2012 ዓ.ም ምንም እንኳን በሎጅስቲክስ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሠራም ሃገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል ባህረኞችን አሰልጥኖ በዓለም ዐቀፍ ተቋማት በማስቀጠር በርካታ ሥራዎችን መሥራት መቻሉን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በብሄራዊ የንግድ መርከብ በዓመት እስከ 7 ሚሊየን ቶን የማጓጓዝ አቅም እንዳላት ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ሃገሪቱ ካላት 11 መርከቦች በተጨማሪ ሁለት ግዙፍ መርከቦችን ለመግዛት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚኖረው አስተዋፅዖኦ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለሥልጣኑ የሃገር ውስጥ ውሃ ትራንስፖርትን ለማስፋፋትና ለመቆጣጠር የሚያስችል የማስተር ፕላን እና የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ታውቋል። ባለሥልጣኑ ካሉት 11 ብሔራዊ የንግድ መርከቦች በተጨማሪ ሁለት ትልልቅ መርከቦች ለመግዛት እንቅስቃሴ እያደረገ ከመሆኑ ባሻገር፣ ኢትዮጵያ በማሪታይም ዘርፍ እያገኘች ያለውን ከ2 ሚሊየን ዶላር ያልበለጠ ገቢ ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል።

LEAVE A REPLY