ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በየከተሞቹ ላይ ጥልቅ ውይይት ያካሄዱ መሆናቸው ተነገረ።
በደሴ እየተካሄደ ባለው ውይይት ላይ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ ነብዩ ስሁል ሚካኤል እና የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዶክተር ዴኤታ ሙሉ ነጋ መገኘታቸው ታውቋል።
ይህን መሰል ተመሳሳይ ዓላማ ያለው ውይይት በባሕር ዳር ከተማም ተካሂዷል። በባሕር ዳር እየተካሄደ ባለው ውይይት የትግራይ ተወላጆች፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎችና ከአዲስ አበባ የመጡ እንግዶች ተሳታፊ ነበሩ ተብሏል።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ እውነታ መረዳት እና መግባባት ላይ መድረስ የውይይቱ ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ በውይይቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ለውይይቶቹ የመነሻ ሰነዶች በጽሑፍ ተዘጋጅተው ቀርበዋል፡፡
ስለኢሕአዴግ ውህደት፣ ስለውህደቱ አስፈላጊነት፣ የህወሓት ከውህደቱ ማፈንገጥ፣ ህወሓት አሁን ያለበት ሁኔታ እና ስለ አፍራሽ እንቅስቃሴው፣ የብልፅግና ፓርቲ ዓላማ እና እሴቶች፣ የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም የትግራይ ሕዝብ ከብልፅግና ፓርቲ አኳያ አሁን ያለበት ነባራዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።