ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በአ/አ ከተማ የነበረውን ኮንትራት ተነጠቀ

ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በአ/አ ከተማ የነበረውን ኮንትራት ተነጠቀ

 ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ተክለብር አምባዬ ኮንስትራክሽን በአዲስ አበባ ከተማ የነበረውን የመንገድ ግንባታ ኮንትራት ተነጠቀ። ኮንስትራክሽን ድርጅቱ በተለያዮ ቦታዎች ያለውን የግንባታ ኮንትራት በቀጣይ ሊነጠቅ እንደሚችልም ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን የግንባታ ስራው ሲከናወን የነበረውን ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ  እስከ ካራ የሚገኘውን የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት ውል ማቋረጡን ይፋ አድርጓል።
ውሉ የተቋረጠው ከሥራ ተቋራጩ ጋር በቅድሚያ የተገባውን ውል መሰረት አድርጎ በተከለሰው የውለታ ጊዜ ውስጥ የፕሮጀክቱን ግንባታ ማጠናቀቅ ባለመቻሉና ተቋራጩ  በፕሮጀክቱ ላይ ባሳየው ደካማ አፈፃፀም (መስከረም 17 ቀን 2013 ነበር መጠናቀቅ የሚገባው) ምክንያት መሆኑንም አስታውቋል።
ባለሥልጣኑ የግንባታ ሥራውን በራስ ኃይል ተረክቦ ቀሪ ሥራውን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት 5.9 ኪ.ሜ የሚሸፍነውን ሙሉውን የአራራት-ኮተቤ -ካራ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ትኩረት የሚሠራ መሆኑ ተነግሯል።
ተክለ ብርሃን አምባዬ በተለያዮ ቦታዎች (ከአዲስ አበባ ውጭ ጭምር) የግንባታ እና የመንገድ ሥራ ውሎችን የፈጸመ ቢሆንም አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች አሁንም በእንጥልጥል ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የጠቆሙ ታማኝ ምንጮቻችን፤ እነዚህ ጉዳዮች በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንና በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እየተገመገሙ መሆናቸውን ተከትሎ በቀጣይም ተቋራጩ ሌሎች ሥራዎችንም በዚህ መንገድ ሊነጠቁ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በደርግ ሥርዓት በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የሕግ ፋክልቲ ዲን የነበሩትና ወያኔ ሀገሩቷን በተቆጣጠረ ማግስት ከሥራ እንዲባረሩ ከተደረጉት 42 የዮንቨርስቲ መምህራን መሀል አንዱ የሆኑት ተክለብርሃን አምባዬ ከተወሰኑ ዓመታት የባህር ማዶ ቆይታ በኋላ ወደኢትዮጵያ በመመለስ ከሥራ ገበታቸው በግፍ ካፈናቀላቸው ሥርዓት ጋር ፍቅር በመሆን በአጭር ጊዜ ዝነኛ ሀብታም ለመሆን መብቃታቸው ይታወሳል።
በያዝነው አመት መንግሥትን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በታክስ አጭበርብረዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የነበረው ባለሀብቱ ተክለብርሃን አምባዬ በመቀሌ ከተማ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ለመገንባት ውል ፈጽመው ወደ ሥራ ከገቡ ስድስት ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን ድረስ ዘመናዊው ስታዲየም በሚፈለገው ደረጃ ሊጠናቀቅ አልቻለም።

LEAVE A REPLY