ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዚህ ወቅት በተለይም የአማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዮ ቦታዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋን ለማጥፋት ጥረት እየደረገ ነው ተባለ።
የግብርና ሚኒስቴር የአንበጣ መንጋ ሥርጭትን ለመቆጣጠር በአውሮፕላን፣ በተሽከርካሪና በሰው ኃይል በመታገዝ የርጭት ሥራ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሥርጭቱን ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ መንጋውን ለመቆጣጠር በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ከየመን፣ ጅቡቲና ሶማሌ ላንድ የተነሳው የአንበጣ መንጋው በኢትዮጵያ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መከሰቱና ከፍተኛ ውድመት ማድረሱ አይዘነጋም።
ሥርጭቱን ለመቆጣጠር አስፈላጊው በጀት ተመድቦ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ማንደፍሮ፣ አሁን ላይ የአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ የብልሽት ችግር ፈተና እንደሆነባቸው አስረድተዋል።
የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል 112 ተሽከርካሪዎች እየሠሩ ሲሆን፣ ለርጭት ሥራው የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት እንዲሁም ጎረቤት ሀገራት ትብብር ለማድረግ ቃል መግባታቸውን እና ስርጭቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 10 አውሮፕላኖች እንደሚያስፈልጉም ተገልጿል።