ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለማዋል የኢትዮጵያ መንግሥት ከሩስያ ጋር ለዐሥር ዓመታት በጋራ ለመሥራት የተደረሰው ስምምነት ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቅረቡ ተነገረ።
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ የኒውክሌር ወይም አውቶሚክ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ውስጥ የኒውክሌር ሕክምና፣ የኒውክሌር ግብርና ቴክኖሎጂ፣ የኒውክሌር ኢንዱስትሪ፣ የጦር መሳሪያና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚገኝበት ለምክር ቤቱ ስምምነቱን ያቀረቡት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ መስፍን ቸርነት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትሆን ከሩስያ መንግሥት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሷ እየተነገረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የኒውክሌር ኢነርጂ መሠረተ ልማት መዘርጋት እንዲችል ሩስያ ድጋፍ እንደምታቀርብም የስምምነት ሰነዱ ያሳያል።
በተጓዳኝ ለኒውክሌርና ለምርምር ማብላያዎች የሚሆን የኒውክሌር ነዳጅ ማቅረብ፣ ለእንስሳትና ለሰው ጤና ጠንቅ የሆነውንና ለአካባቢም አሉታዊ እክል የሚፈጥሩ ራዲዮ አክቲቭ ዝቃጮችን ለማስወገድም የሩስያ መንግሥት እገዛ እንደሚያደርግም ከስምምነቱ መረዳት ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ ላይ ለሚሠማሩ ኢትዮጵያውያንም ሩስያ ሥልጠና ለመስጠት የተስማማች መሆኑን የጠቆመው ዜና፣ የሚሰለጥኑ ሠራተኞችም በኢንዱስትሪ፣ በሕክምናና በግብርና ዘርፍ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ተጠቅመው እንዲሠሩ የሚጠበቅባቸው መሆኑም ተነግሯል።
ለ10 ዓመት የሚዘልቅ ነው የተባለው ይህ ሰምምነት በዝርዝር እንዲመረምር በምክር ቤቱ ለውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ታውቋል።