ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነገረ።
በተለይም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን የሚያሳይ ምስልና የባለሰቆቃዎቹ ኢንተርቪ በተለያዮ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ከተለቀቀ በኋላ መንግሥት ዜጎቹን እንዲያወጣ ግፊት ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት የመመለሱ ሂደት አካል የሆኑ 297 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ከሳዑዲ አረቢያ መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
ጽሕፈት ቤቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው አጠር ያለ መሠረት ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን መካከል ሃያ አምስቱ ሕፃናት ሲሆኑ፤ ከአሰቃቂው ስደት ተመላሽ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ከአውሮፕላን ሲወርዱ ተንበርክከው መሬት ሲስሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከለቀቃቸው ምስሎች ላይ ተመልክተናል።