የትግራይ ም/ፕሬዝዳንት የበጀት እግዱ በትግራይ ሕዝብና ክልል ላይ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል አሉ

የትግራይ ም/ፕሬዝዳንት የበጀት እግዱ በትግራይ ሕዝብና ክልል ላይ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገወጥ መንገድ የተቋቋመ ነው ላለው የትግራይ ክልል ም/ቤትና ካቢኔ የፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ እንደማያደርግ መወሰኑ ክልሉን ከፌዴሬሽኑ እንዲወጣ የሚገፋ መሆኑን የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብርሃም ተከስተ ገለፁ።

ውሳኔው እስካሁን ሲወሰድ የነበረው ሕገወጥ እርምጃ  ቀጣይ አካል እንደሆነ የጠቆሙት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ እርምጃው ሓላፊነት የጎደለው ከመሆኑ በተጨማሪ የትግራይ ክልልን ከፌዴሬሽኑ እንዲወጣ የሚገፋ እንደሆነም አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ የፌደራል መንግሥት ከክልሎች ከሚሰበስበው ገቢ ላይ ለትግራይ ክልል መንግሥት ድጎማ እንዳይሰጥ ውሳኔ ማሳለፉ በሌላ አገላለጽ ትግራይ የፌዴሬሽኑ አካል አይደለችም እንደ ማለት ነው ያሉት በቅርቡ ከክልላዊው ምርጫ በኋላ የደብረፂዮን ምክትል ሆነው የተሾሙት ዶክተር አብርሃም፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ውሳኔ በትግራይ ክልልና ሕዝብ ላይ ጦርነት እንደማወጅ አድርገው እንደሚቆጥሩት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ እና የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥታት አንዱ የሚያገናኛቸው የበጀት ሥርዓቱ ነው ያሉት እኚህ የህወሓት ከፍተኛ አመራር፤  “ትግራይ ክልል የፌዴሬሽኑ አባል ናት፣ እርምጃውም ፌዴሬሽኑን የሚበትን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ውሳኔውን በጣም አደገኛ ያሉት ዶክተር አብረሃም ፣ አገሪቷን ወደ ቀውስ የሚያስገባ፣ የሚበትን ፣ እንዲሁም ሓላፊነት የጎደለው እርምጃ እንደሆነ ከመናገራቸው ባሻገር፣ የፌደራል መንግሥት ገቢ የሚሰበስበው ትግራይን ጨምሮ ከክልሎች ስለሆነ ይሄንን መልሶ ለክልሎች ማከፋፈል ግዴታው ነው ብለዋል።
“ከትግራይ የሚሰበስበውን ገቢ ለትግራይ አላካፍልም ማለት እብደት ነው” ያሉት የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ እንዳለው ወደዚህ እርምጃ የሚገባ ከሆነ የትግራይ ክልል ራሱን ያገላል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

LEAVE A REPLY