ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ ለአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የዐሥር ቀናት አበል ክፍያ እንዲፈጸምላቸው የቀረበውን ደብዳቤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አልፈርምም ማለታቸው ተሰማ።
መስከረም 23 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የተከበረውን የኢሬቻ ዋዜማ ወይም ሆረ ፊንፊኔን አስመልክቶ አርብና ቅዳሜን ጨምሮ ሁሉም የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጋቸውን ተከትሎ ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአንድ አበል የዐሥር ቀን ክፍያ (ከአምስት ሺኅ ብር በላይ) ለመክፈል እንዲችል የፍቃድ መጠየቂያ ደብዳቤ ያስገባው።
ፖሊስ ቤት ውስጥ ይህ አይነቱ አሠራር የተለመደ መሆኑን የተናገሩና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ የዜና ምንጮች ባለፍው ዓመት በተከበረው የኢሬቻ በዓል ማግስት ኢ/ር ታከለ ኡማ እንደየደምዎዛቸውና ሓላፊነታቸው እርከን ለሁሉም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የ15 ቀን ክፍያ መፈጸማቸውን አስታውሰዋል።
ከዛ ቀደም ባሉት ጊዜያት የአርበኞች ግንቦት ሠባት አመራሮችና የኦነግ አባላት ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ የአዲስ አበባ ፖሊሶች የ15 ቀን አበል በታከለ ኡማ ተፈቅዶላቸው እንደነበር የሚናገሩት የፖሊስ አባላቱ አሁን ላይ ለአዳነች አቤቤ የቀረበው የውሎ አበል ክፍያ በአምስት ቀን ተቀንሶ የ10 ቀን እንዲሆን የተደረገው የኮቪድ ወረርሽኝን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አስረድተዋል።
ለአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የቀረበውን የዐሥር ቀን አበል ፍቃድ ደብዳቤ አልፈርምም በማለት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ውድቅ ያደረጉት ከአምስት ቀን በፊት (ሰኞ ዕለት) እንደነበረ የጠቆሙት ምንጮቻችን ከንቲባዋ ለፖሊስ ኮሚሽኑ አመራሮች (ምንም ዓይነት የአበል ክፍያ አያስፈልግም፣ ፖሊሶቹ ሥራቸውን ነው የሠሩት። በአመት አንዴና ሁለቴ ይሄን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሁሌም እንዲህ አይነት ጠንካራ ሥራ መሥራት ይገባቸዋል” የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም አረጋግጠዋል።
አመራሮቹ እንዲህ አይነቱ የአበል ክፍያ በታከለ ኡማ ጊዜ የሚፈጸም መሆኑን ለማስረዳት ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱንም ከታማኝ ምንጮቻችን መረዳት ችለናል።