ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አሁን በኢትዮጵያ ያለውን አለመረጋጋት በመመካከር እና በመነጋገር እንዲፈታ ቤተክርስትያን ጠንክራ መሥራት እንደሚጠበቅባት ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለፁ።
39ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሰበካ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘእክሱም ወዕጨጌ ተክለሃይማኖት ርዕሰ መንበር፤ ኢትየጵያ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት በመመካከር፣ በመነጋገር እንዲፈታ ቤተክርስትያን ጠንክራ ትልቅ ሥራ ማከናወን ይኖርባታል ብለዋል።
በተደጋጋሚ በተከሰተ አለመረጋጋት ለተጎዱ ወገኖች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ህዝበ ክርስትያንን ድጋፍ ማድረግ የተሞከረ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር እርዳታው በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል።
የአንበጣ መንጋ እና በሀገሪቱ ያሉት ችግሮችን ከቤተክርስትያን ጋር በመሆን ማስቆም እንደሚገባ የጠቆሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ሥራ አጥነት በመበራከቱ ወጣቶች በውጭ ሀገራት ተሰደው ለህልፈት፣ ለሰብኣዊ ጥቃት ፣ እንዲሁም ለእስር ቤት መዳረጋቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ተቋማት የሚመለከታቸው አካላት፣ መንግሥት ጨምሮ በስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸውም ፓትሪያርኩ አሳስበዋል።