ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ ተከራከሩ።
በድምጻዊው ግድያጨተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙት አራቱ ተጠርጣሪዎች ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ፣ አብዲ አለማየሁ እና ላምሮት ከማል ሁሉም ወንጀሉን አልፈጸምንም፣ ጥፋትም የለንም በማለት ዛሬ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕግ እና ጸረ ሽብር ችሎት ዛሬ (ረቡዕ ) በቀረቡበት ወቅት ይህን መከራከሪያ ያነሱት ተጠርጣሪዎቹ፤ ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት ቀርበው በነበረበት ወቅት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የማቆም አቅሙ የለንም ያሉ ሲሆን፤ 4ኛ ተጠርጣሪ ላምሮት ከማል በበኩሏ ጠበቃ ለማቆም ብፈልግም ሊወክለኝ ፍቃደኛ የሆነ ጠበቃ ላገኝ አልቻልኩም ማለታቸው ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከላካይ ጠበቆች የተመደቡ ጠበቃ ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤
ሆኖም የተመደቡት ጠበቃ የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 20.5ን በመጥቀስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ላሉት ተከሳሾች መቆም እንደሚችሉ ገልጸው፣ 4ኛዋ ተከሳሽ ላምሮት ከማልን ለመወከል የተሰጣቸው ውክልና እንዲነሳ ጠይቀዋል።
አራተኛዋ ተከሳሽ ፍቃደኛ ሆኖ የሚቆምላት ጠበቃ አጣች እንጂ ጠበቃ የማቆም አቅም አላነሳትም ስለዚህም ውክልናችን ትክክል አይደለም ሲሉ ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱ የጠበቃውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ መንግሥት የመደባቸው ጠበቃ አራተኛዋ ተከሳሽንም እንዲወክሉ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተከሳሾች ጠበቃ ተከሳሾቹ የክስ መከላከያ እንደሌላቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕግም ፖሊስ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ቢጠይቅም፣ ፍርድ ቤቱ ግን ዐቃቤ ሕግ ራሱ ምስክሮቹን ከኅዳር 23 እስከ 25/2013 ዓ.ም ምስክሮቹን ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።