የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ተባባሪ ባለመሆኑ የአንበጣ መንጋው ላይ ኬሚካል መርጨት አልተቻለም...

የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ተባባሪ ባለመሆኑ የአንበጣ መንጋው ላይ ኬሚካል መርጨት አልተቻለም ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ የአንበጣ መንጋው ላይ የኬሚካል ርጭት ለማድረግ አስፈላጊ መረጃዎችን ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ በትግራይ ክልል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል እርጭት ማካሄድ አለመቻሉን የግብርና ሚንስቴር ገለፀ።

የአንበጣ መንጋውን ለመዋጋት ሚኒስቴሩ አውሮፕላኖችን ጨምሮ የአንበጣ መከላከያ መሳሪያዎችን ቢያዘጋጅም ፣ የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮም ይሁን እስከ ወረዳ ያሉት መዋቅሮች የአንበጣውን መገኛ አሳውቆ እርጭት እንዲደረግ የፍቃደኝነት ችግር እንደታየባቸው በግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ ለማ ተናግረዋል።
በዚህ የተነሳ የአንበጣ መንጋ በትግራይ ክልል ቢከሰትም እስካሁን የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ አለመቻሉን የጠቆሙት ሓላፊው፤ አሁንም ቢሆን ችግሩን ለመቅረፍ ከክልሉ ወረዳዎች ጋር በስልክ እየተገናኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ወረዳዎቹ የአንበጣ መንጋው የተከሰተበትን ቦታ ለይተው የሚያሳወቁ ከሆነ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ማድረግ እንደሚቻልም የግብርና ሚኒስቴር ዝግጁ መሆኑ ነው የተነገረው።
የገበሬው ምርት ከፖለቲካ የተለየ ነገር መሆኑን የገለፁት የሕዝብ ግነኙነት ዳይሬክተሩ አመራሮቹ ፋይዳውን አይተውና ለሕብረተሰቡ አስበው መረጃውን የሚሰጡ ከሆነ የፌደራል መንግሥት የኬሚካል ርጭቱን ለማካሄድ ፍላጎቱ እንዳለው ይፋ አድርገዋል።
በጉዳዮ ላይ ምላሽ ለቢቢሲ የሰጠው የትግራይ ክልል በበኩሉ ከግብርና ሚኒስቴር የኬሚካል እርጭት የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች ለይተው እንዲያሳውቁ ጥያቄ እንደቀረበላቸው አረጋግጧል።
በትግራይ ክልል የእርሻና ገጠር ልማት ቢሮ የተምች መከላከልና ቁጥጥር፣ የዕፅዋት ኳራንታይን ዳይሬክተር አቶ መብራህቶም ገብረኪዳን የግብርና ሚንስቴር በአውሮፕላን አማካኝነት የኬሚካል እርጭት ለማካሄድ መጠየቁን ባይክድም፤ “አውሮፕላን እንደሚልኩና የሚረጭበት አካባቢ እንድናሳውቃቸው በነገሩን መሠረት ስምምነት ላይ የደረሰንም ቢሆንም፣ ግን እምነት የለንም” የሚል አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY