የፍትህ መጽሔት ባለቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታሰረ

የፍትህ መጽሔት ባለቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታሰረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የተወዳጇ ፍትህ መጽሔት ባለቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለእስር መዳረጉ ተሰማ።

በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ባለፉት ዐሥር ዓመታት ጎልተው መውጣት ከቻሉ ጥቂት ጋዜጠኞች መሀል ግንባር ቀደም የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በአዳነች አቤቤ ጉዳይ ክስ የመሠረተበት የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ እንደሆነ ተገምቷል።
ባለፈው ቅዳሜ ለኅትመት በበቃችው ፍትህ መጽሔት ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው በተሾሙት በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የባንክ አካውንት ላይ 40 ሚሊዮን ብር መገኘቱን ያስነበበው ተመስገን ደሳለኝ ላይ ክስ እንዲመሠረት ለፖሊስና ለብሮድካስት ባለሥልጣን አዳነች አቤቤ ደብዳቤ መጻፋቸውን ታማኝ ምንጮች ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል።
ተመስገን ደሳለኝ በዚህ ጽሑፉ  ከንቲባዋ በኦዴፓ አመራሮች ስብሰባ ላይ ቀድሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የነበሩትና ከሓላፊነታቸው በተነሱት በአቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በባንክ አካውንታቸው ውስጥ የተገኘውን 40 ሚሊዮን ብር ከየት እንዳመጡት ሲጠየቁ ” አካውንቴ ውስጥ ማን እንደከተተው አላውቅም ” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስነብቦ ነበር።
ይህን ተከትሎ ዛሬ ከሰዐት በኋላ በሁለት መኪኖች የተጫኑ በርካታ ፖሊሶች አደዋ ድልድይ አካባቢ የሚገኘው የፍትህ መጽሔት ቢሮን ከበው ጋዜጠኛውን ለመውሰድ ቢሞክሩም ተመስገን በሰዐቱ ቢሮ ውስጥ ስላልነበር ሊያገኙት አልቻሉም ነበር።
ይሁንና ፖሊሶቹ ስልክ ደውለው በጠሩት መሠረት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወስደውታል። የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እስከ ምሽት 12፡ 30 ድረስ ከእስር አልተፈታም። ጋዜጠኛው በተመሠረተበት ክስ ነገ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል ተገምቷል።

LEAVE A REPLY