ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከ44 ዓመት በፊት ህወሓትን የመሠረቱት፣ በመለስ ዜናዊና በስብሐት ነጋ ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት እንዲባረሩ የተደረጉት ዶክተር አረጋዊ በርሄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትልቅ ሹመት ተሰጣቸው።
ከህወሓት የበረሃ የትጥቅ ትግል የተባረሩት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ድርጅቱ ከጫካ ወደ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ከገባ በኋላ የትግራይ ሕዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ እንደ አንድ የማፍያ ቡድን የጥቂት ግለሰቦችና ቤተሰቦቻቸውን ሀብት የማካበት ተግባር እያከናወነ መሆኑን ሲያጋልጡ እንደነበር ይታወሳል።
በለውጡ ማግስት በስደት ሕይወት አብረዋቸው ከነበሩት የትግል አጋራቸው ዶ/ር ኢንጂነር ግደይ ዘርዓፂዮን ጋር የመሠረቱት ትዴት (የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር) ፓርቲን ይዘው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ ሀገር ቤት የገቡት አረጋዊ በርሄ ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጥቅምት 04 /2013 ዓ.ም ጀምሮ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል።
በህወሓት መራሹ መንግሥትም ሆነ በለውጡ ቡድን ውስጥ እስካሁን ድረስ ይህንን ቦታ በሓላፊነት ሲመሩ የነበሩት የህወሓት አባሏ ወ/ሮ ሮማን ገብረሥላሴ፤ መቀሌ የመሸገው ቡድን ከመስከረም 25 በኋላ በፌደራል ሥልጣን ላይ ያሉ አባሎቹ ሓላፊነታቸውን እንዲለቁ ባሳሰበው መሠረት ግለሰቧ ከተሰጣቸው ትልቅ ሥልጣን የመንሸራተት አዝማሚያ ማሳየታቸውን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቦታቸው እንዲነሱ ተደርገዋል ነው የተባለው።