ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጥቃቶች በበዙበት በቤንሻንጉል ዞን መተከል ዞን ስር ባሉ ሠባት ወረዳዎች የሚሊሻ ስልጠና መሰጠቱን እና አዳዲስ የሚሊሻ አባሎችም እየተመለመሉ መሆኑ ታወቀ።
የክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን አካባቢ አሁን በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመደበኛ የሕግ ማስከበር ብቻ መቆጣጠር የሚቻል ባለመሆኑ ከመስከረም 11ቀን 2013 ዓ. ም ጀምሮ ለሦስት ወራት የሚቆይ የኮማንድ ፖስት መታወጁን ገልጸዋል።
የኮማንድ ፖስቱ በመከላከያ ሠራዊት የሚመራ ሲሆን፣ የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ በጋራ ሰላም የማስከበሩን ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ለቢቢሲ የተናገሩት ሓላፊው፤ በዞኑ ከዚህ ቀደም የነበሩ የሚሊሻ አባላት፣ እንዲሁም አዲስ ምልመላ ተካሂዶ ሥልጠናው ላለፉት ሦስት ቀናት እየተሰጠ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
በዞኑ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የተመለመሉት እነዚህ የሚሊሻ አባላት፣ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እንደተውጣጡና ከስልጠናውም በኋላ በቂ ትጥቅ በማስታጠቅ የፀጥታ መዋቅሩን እንዲደግፉ እንደሚደረግ ነው የተገለጸው።
ቀደም ባሉት ዓመታት የሚሊሻ አባል የነበሩና እድሜያቸው ያልገፉ አባላት በአሁኑ ሥልጠና ላይም እንዲካተቱ መደረጉን የተናገሩት ሓላፊው እንደየቀበሌው ስፋት ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ አዳዲስ አባላት መመልመላቸውን ከመናገራቸው ባሻገር፣ ምልመላው የብሔር ብሔረሰቦችን ተዋፅኦ የጠበቀ መሆኑንም እና ስልጠናው ለተከታታይ ሶስት ቀናት በመከላከያ ሠራዊት አባላት እና ፖሊሶች መሰጠቱን ይፋ አድርገዋል።