ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ ባለፉት 21 ቀናት በርካታ የውጭ ግንኙነት ተግባራት ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
ባለፉት 3 ሳምንታት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ መቀጠል በምትችልበት ጉዳይ ላይ ሀሳብ መቅረቡን የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም 37ኛው የአፍካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ መካሄዱንም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በውይይቱ ከአባል ሀገራት ከሚገኝ መዋጮ በተጨማሪ ሌሎች ገቢ ማስገኘት የሚቻልባቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ምክክር የተደረገ ከመደረጉ ባሻገር የሕብረቱ ቀጣይ እቅድና አቅጣጫዎች ላይም ምክክር መደረጉ ተሰምቷል።
በተጠቀሱት 21 ቀናት ውስጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን አቅንቶ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መክሯል ነው የተባለው።
በሌላም በኩል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዘጠኝ ሃገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ የተቀበሉ ሲሆን፣ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንም በኢትዮጵያ ከተሾሙ አዳዲስ አምባሳደሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በተያያዘ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ 993 ኢትዮጵያን ከስደት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ እንደሆነ ያስረዱት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ሌሎችንም ወደሃገራቸው ለለመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።