ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፌዴራል ሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሀብት እና ንብረታቸውን ያላስመዘገቡ 100 የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች አስፈላጊው የሕግ ማጣራት እንዲደረግባቸው የስም ዝርዝርቸውን ለፌዴራል ፖሊስ እንደሚያስተላልፍ ይፋ አደረገ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች አንድ ሺኅ ብር እየተቀጡ ሀብት እና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ዛሬ 11 ሰዐት ከ30 ላይ መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።
አስቀድሞ በተለያያ ጊዜ በተነገረው ማሳሰቢያና በተሰጠው የጊዜ ገደብ ሀብት ንብረታቸውን ካላስመዘገቡ 180 የፌዴራል መንግሥት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ሓላፊዎች መካከል 80ዎቹ አንድ ሺኀ ብር የቅጣት መቀጮ ተጥሎባቸው ሀብት ንብረታቸውን ማስመዝገባቸውን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ቀሪዎቹ 100 የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ግን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሀብት ንብረታቸውን ባለማስዘግባቸው አስፈላጊው የሕግ ማጣራት እንዲደረግባቸው ለፌዴራል ፖሊስ የስም ዝርዝራቸው እንደሚተላለፍ ገልጸዋል።