የእንቦጭ አረምን በአንድ ወር ከጣና ሐይቅ ለማጥፋት ነገ ይፋዊ ዘመቻ ይጀመራል ተባለ

የእንቦጭ አረምን በአንድ ወር ከጣና ሐይቅ ለማጥፋት ነገ ይፋዊ ዘመቻ ይጀመራል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በአንድ ወር ዘመቻ ለማጥፋት ከነገ ሰኞ ጀምሮ ወደ ሥራ ይገባል ተባለ።

የእንቦጭ አረምን የማስወገድ ዘመቻው የሚከናወነው ከጥቅምት 09 እስከ ህዳር 09/2013 ዓ.ም መሆኑን የገለጹት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዮኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ የጣና ሐይቅን መጠበቅ እና ከአደጋ ነጻ መሆን አለበት የሚል መርህ ክልሉ መያዙንም ገልፀዋል።
ነገ በይፋ የሚጀመረው የ ዘመቻ ዓላማ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጣናን ከእምቦጭ በመታደግ ወደነበረበት መመለስ እና የህዳሴ ግድብንም ከእምቦጭ አረም ስጋት ነጻ ማድረግ እንደሆነም ሓላፊው አስረድተዋል።
በአማራ ክልል ጣና ሐይቅ አካባቢ በሦስት ዞኖች፤ 9 ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በ30 ቀበሌዎች ላይ የእምቦጭ አረሙ ተስፋፍቶ 4 ሺኅ 300 ሄክታር የሚሆነው የሐይቁን ክፍልም አረሙ እንደወረረው አሁን ላይ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ክልሉ ሐይቁንና ሌሎች የውሃ ውስጥ አካላትን የማልማት እና የመጠበቅ ሓላፊነት የተሰጠው በመሆኑ፤ ኤጄንሲ ከማቋቋም ባለፈ በበጀት እና የሰው ሀይል በመመደብ በተለያየ ጊዜ ሐይቁን ከእምቦጭ ለመከላከል መሥራቱን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም አረሙ እንዳይስፋፋ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም ሆኖም እምቦጭን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በአካባቢው ማኅበረሰብ እና ክልል ብቻ ማሳካት እንደማይቻል አስረድተዋል።
ነገ የሚጀመረው የአንድ ወር ዘመቻ ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላት፣ የሲቪክ ማኅበራት እና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እምቦጭ የሚገኝባቸውን ቀበሌዎች እና ወረዳዎች በመከፋፈል በቀን ከ250 እስከ 300 ሰው በየቀበሌው የሚሠማራ ሲሆን ይህንን የሚያስፈጽም ኮሚቴም ተቋቁሟል። ለዘመቻው 106 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ይህንንም ከተለያዩ አካላት ለማሰባሰብ እቅድ ተይዟል።

LEAVE A REPLY