አቶ ልደቱን የኦሮሚያ ፖሊስ ዛሬውኑ ከእስር እንዲፈታ በድጋሚ ቢታዘዝም እስከ አሁን አልተለቀቁም

አቶ ልደቱን የኦሮሚያ ፖሊስ ዛሬውኑ ከእስር እንዲፈታ በድጋሚ ቢታዘዝም እስከ አሁን አልተለቀቁም

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የፍርድ ቤት ውሳኔን ብቻ ሳይሆን ህግን በተደጋጋሚ የጣሰው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አቶ ልደቱ አያሌውን ዛሬውኑ እንዲለቃቸው በድጋሚ ቢታዘዝም አቶ ልደቱ እስካሁን ድረስ እንዳልተፈቱ ታውቋል።

ዛሬ የተሰየመው የምክራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኦሮምያ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬውኑ አቶ ልደቱን እንዲለቃቸው  ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም እስከ ምሽቱ 12፡ 30  ድረስ ከእስር  አለመለቀቃቸውን ኢትዮጵያ ነገ ከኢዴፓ ሊቀመንበር  ከሆኑት አቶ አዳነ ታደሰ መረዳት ችላለች።
ከሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በቢሾፍቱ ከተማ ለተነሳው ግርግርና ኹከት እገዛ አድርገዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት ልደቱ አያሌውን የኦሮሚያ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ፤ በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ያስተላለፈው መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።
ሆኖም የኦሮምያ ፖሊስ የተለያዮ ምክንያቶች በመፍጠር እስካሁን ሳይለቃቸው ቀርቷል። የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ችሎት የኦሮምያ ፖሊስ ኮሚሽን አቶ ልደቱን ለምን እንደማይለቅ እንዲያስረዳ በጠየቀው መሠረት፣ የኮሚሽኑ ሓላፊ ከሕገ ወጥ መሣሪያ ጋር በተያያዘ ሌላ ክስ እንደተመሠረተባቸው በመግለፅ ያቀረቡት ሰበብ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የፖሊስ ኮሚሽን ሓላፊው ዛሬውኑ አቶ ልደቱን ለቀው፣ ከነገ በስቲያ ለፍ/ቤቱ ሪፖርት እንዲያደርጉ፤  ይህንን ካላደረጉ ግን ፍ/ቤቱ እርምጃ እንደሚወስድባቸው ትእዛዝ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ፈጽሞ ለሕግ ተገዢ መሆን ያልፈለገ የሚመስለው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እስከ አመሻሹ ድረስ አቶ ልደቱ አያሌውን አለመልቀቁ ታውቋል።

LEAVE A REPLY